በእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፍ በሲቪልና መስኖ ስራዎች መምሪያ የድሬይን አፈር የማንሳት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፍ ስር በሚገኙት የመሬት ዝግጅት እና የሲቪልና መስኖ የስራ ክፍል በቅንጅት በሚሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ ለረጅም ዓመታት በድሬይን ላይ ተከማችቶ የነበረውን ደለል አፈር በማንሳት የሸንኮራ አገዳ ማሳዎች ላይ የማስገባት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የደለል አፈር የማንሳት ስራው እየተከናወነ የሚገኘው ከሸዋ አለምጤና ድልድይ እስከ ጬካ አለምጤና የማሳ ቁጥር 159 ባለው መካከል ሲሆን ከፊልድ 87፣110 እና121 ቁጥር ድሬይን ላይ በአጠቃላይ የፋብሪካውን ማሽነሪ በመጠቀም 1,175 ሜትር ርዝመት ያህል የድሬይን አፈር የማንሳት እንዲሁም በኪራይ ዶዘር እና ሾርትሪች ስካባተር በመጠቀም 765 ሜትር
የድሬይን አፈር በማንሳት ስታንዳርዱን የጠበቀ የድሬይን ቁፋሮ ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን
ተ/የሲቪል ስራዎች ቡድን መሪ አቶ አለማየው ኦዳ ተናግረዋል፡፡
የአገዳ ተከላ እና እንክብካቤ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ እድሪስ የሱፍ ከስራው ጋር አያይዘው እንደተናገሩት የአገዳ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ከሚተገበሩት ስራዎች አንዱ የደለል አፈርን ወደ ማሳ በማስገባት የአፈሩን ፊዚካልና ኬሚካል ይዘትን በማሻሻል የአገዳ ምርታማነትን መጨመር በመሆኑ በሲቪልና መስኖ ስራዎች እየተተገበረ ያለውን የድሬይን አፈር ወደ ማሳ የማስገባት ስራ ጉልህ ሚና እንዳለው በመግለፅ በቅንጅት ስለተሰራው ሥራ ለክፍሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ተ/የሲቪል እና መስኖ ስራዎች ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ሀይሉ ስራወን አስመልክቶ እንደተናገሩት ድሬይን ላይ ያለው አፈር ከዚህ በፊት ለረጅም ዓመታት ከድሬይን ውስጥ በቁፋሮ የወጣና የተከመረ በመሆኑ ማሽነሪው በሚፈለገው ልክ አፈሩን ቆፍሮ ለማውጣት ስለራቀው ስታንዳርዱን መጠበቅ አለተቻለም፡፡ አሁን ግን በየድሬይኑ ዳርቻ ላይ ያለውን አፈር ማንሳታችን በርካታ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ይህም ስታንዳርድን ጠብቀን በጥልቀት የድሬይን ቁፋሮ ለማካሄድ፣በደለል አፈር መብዛት ምክንያት በአርሶ አደር የእርሻ ማሳ ላይ የሚተኛውን የዝናብ ውሃ ለመከላከል፣ከድሬይን ላይ የተነሳውን አፈር ምርታማነታቸውን የቀነሱ ማሳዎች ውስጥ በማስገባት የአገዳ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር፣ ክረምት በመጣ ቁጥር የጎርፍ ውሃ ወደኋላ ተመልሶ የሸዋ መኖሪያ ሰፈር እንዳይገባ ለመከላከል እንዲሁም በዚሁ ምክንያት ከልማቱ ወጥቶ የነበረውን የፋብሪካው ይዞታ የሆነው ከ750 ሄክታር በላይ የሆነ የሸንኮራ አገዳ ማሳ ወደ ልማቱ ለመመለስ መሆኑን ገልፀው ለዚህ ስራ መሳካት ማኔጅመንቱ ተጨማሪ ማሽነሪዎችን በመከራየቱ አመስግነዋል፡፡