የቀዩ ዝሆን አዲስ ከፍታ—በዓለም አቀፍ ጥራት!!

የወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የዓለም አቀፍ የጥራት ማኔጅመንት ስርዓት QMS ISO-9001:2015 የምስክር ወረቀት ማግኘቱን ተከትሎ፣ በፋብሪካው ግቢ ውስጥ ደማቅ የዕውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሄደ። በፕሮግራሙ ላይ የማኔጅመንት አባላት፣ ሰራተኞች እና የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ተወካዮች በተገኙበት ይህ ታሪካዊ የምስራች በይፋ ተበስሯል።
ፋብሪካው በሁሉም የሥራ ሂደቶች ውስጥ ሲስተሙ የሚያስቀምጣቸውን መስፈርቶች በተሟላ ሁኔታ መተግበሩ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ከተገመገመ በኋላ፣ ይህን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘት በቅቷል።
በዕለቱ የዋና ስራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢዩኤል ለላንጎ ሂደቱን አስመልክተው ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል። በሪፖርታቸውም የስኬቱን ጉዞ፣ የታዩ ጠንካራ ጎኖችንና ተግዳሮቶችን በዝርዝር ዳስሰዋል። ለአብነትም፦
• የከፍተኛ አመራሩ ቁርጠኝነትና ለደንበኞች ትኩረት መስጠት፣
• ለትግበራው የሚያስፈልገውን ሀብትና በጀት መመደብ፣
• ተቋማዊ ተግባራትን እንደ አንድ የተሳሰረ ሂደት በመመልከት ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ፣
• ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን አስቀድሞ በመለየት የመከላከያ መንገዶችን መቀየስ፣
• የአሰራር መመሪያዎችን፣ ፖሊሲዎችንና የሥራ አፈጻጸም ማስረጃዎችን (Documented Information) በሥርዓት መያዝ፣
• ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም ቀጣይነት ያለው መሻሻል (Continual Improvement) ማረጋገጥ ለውጤቱ መገኘት ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል።
አቶ ኢዩኤል አክለውም ይህ ስኬት በአንድ ጀምበር የመጣ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ጥረት ውጤት መሆኑን አስታውሰዋል። ፋብሪካው ይህን ዕውቅና ለማግኘት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮና በስኳር ኮርፖሬሽን ስር በነበረበት ወቅትም በተለያዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ ጥረቶችን በማድረግ ይህን የምስክር ወረቀት ለማግኘት ቢደክምም፣ በተለያዩ ተግዳሮቶች ሳይሳካ መቆየቱን አስታውሰዋል። 
 
ዘንድሮ ግን በአመራሩና በሠራተኛው የጋራ ርብርብ፣ በበጀት አቅርቦትና ወቅታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የታዩ ውስንነቶችን በመቅረፍ “በዘርፉ የመጀመሪያውን QMS ISO-9001:2015 የምስክር ወረቀት በማግኘታችን እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት የደስታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።የወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክትና የስራ አቅጣጫ፡ ለዚህ ስኬት መብቃት ለማኔጅመንት አባላትና ለባለሙያዎች የተሰጡ ተከታታይ ስልጠናዎች ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው ገልጸዋል። ሂደቱ አድካሚና ፈታኝ ቢሆንም በጽናት ማለፍ መቻሉን ጠቁመዋል።
አቶ ሰለሞን “ይህ ድል የበለጠ እንድንተጋ የሞራል ስንቅ ሊሆነን ይገባል” በማለት፣ የጥራት ኦዲተሮች የሰጡት አስተያየት ለፋብሪካው ትልቅ ትምህርት ከመሆኑም ባለፈ ለሌሎች ፋብሪካዎች እንደ ተሞክሮ የሚቀመር መሆኑን ገልጸዋል። ውጤቱን በዘላቂነት ለማስቀጠልም መሬት ላይ ያሉ ተግባራትን በተከታታይ መገምገም እንደሚገባ አሳስበዋል። በመጨረሻም ለመላው የፋብሪካው አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ ባለድርሻ አካላት እና በተለይም ለሠራተኛ ማህበሩ ላደረጉት ልዩ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ በደመቀ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን፣ የስኬቱ መታሰቢያ የሆነው የኬክ መቁረስ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል። በተጨማሪም ለዚህ ታላቅ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የዘርፍና የመምሪያ ሥራ አስኪያጆች፣ ለውስጥና ለውጭ ኦዲተሮች እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም መርሃ ግብሩ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ላደረጉ የስርዓተ ፆታና ወጣቶች የስራ ክፍልና ሴት አምባሳደሮች ምስጋና አቅርበዋል።
Scroll to Top