WONJI SHOA SUGAR FACTORY
OFFICIAL NEWS & UPDATES
NEWS / ANNOUNCEMENTS
Company News and Official Announcements
By Communications Office
·
የወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ለመጪው ምርት ዘመን የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ሲያካሂድ የቆየውን አጠቃላይ የክረምት ጥገና በውጤታማነት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ። ለ17 ሳምንታት ታቅዶ ሲተገበር በቆየው በዚህ የጥገና መርሐ ግብር እስካሁን 15 ሳምንታት ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ ሲሆን፣ ፋብሪካው አሁን ወደ ‘Test and commissioning’ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል።
የፋብሪካው ዘርፍ ቴክኒክ መመሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ደፋሩ እንደገለጹት፤ የጥገና ሥራዎቹ የተጀመሩት በቀድሞ የኦፕሬሽን ወቅት ያጋጠሙ ክፍተቶችን በጥንቃቄ በመለየትና የተቀናጀ አጠቃላይ ዕቅድ በማዘጋጀት ነው። በዚህም መሠረት የውስጥ አቅምን እና ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በተለይም ቀደም ሲል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬና ወጪ ይከናወኑ የነበሩ ውስብስብ ጥገናዎች በፋብሪካው አመራሮች፣ ሠራተኞች እና በፋብሪኬሽን ወርክሾፕ ባለሙያዎች ቅንጅት በራስ አቅም መከናወናቸው ተገልጿል። በዚህም በየፋብሪካው ክፍሎች የሚከናወኑ የሜካኒካል፣ የኤሌክትሪካል እና የኢንስትሩመንቴሽን (Mechanical, electrical, and instrumentation) ሥራዎች፣ እንዲሁም የፓምፖች እና ጊርቦክሶች (Pumps and gearboxes) ጥገና ከወርክሾፕ ጋር በመቀናጀት በጥሩ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል በዋናነት የዶር (Dorr)፣ ትራሽፕሌት (Trashplate)፣ ቤሪንግ ላይነር (Bearing liner) እና ሌሎች መለዋወጫዎች በራስ አቅም ተሠርተው ለውጤት መብቃታቸው ተጠቃሽ ነው።
ለዚህ ስኬት መመዝገብ የማኔጅመንት ቡድኑ በየሳምንቱ የሚያደርገው ጥብቅ ክትትል፣ የአቅርቦት ክፍተቶችን በአንድ መድረክ በመገምገም ወቅታዊ ውሳኔዎችን ማስተላለፉ እና የግዢ ዕቃዎችን ጥራት በኦዲት ማረጋገጡ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ከዚህም ባሻገር በሠራተኛውና በሥራ መሪው መካከል የተፈጠረው ከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት ለውጤቱ መሠረት መሆኑ ተገልጿል።
ፋብሪካው በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ሙሉ በሙሉ ወደ ሁለገብ የሙከራ ሥራ (Test and Commissioning) የሚገባ ሲሆን፣ በሂደቱ የሚታዩ ጥቃቅን ጉድለቶች ተስተካክለው ወደ መደበኛ ምርት እንደሚገባ ታውቋል። የቴክኒክ መምሪያ ሥራ አስኪያጁ አቶ አበበ ደፋሩ በሂደቱ ንቁ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ላሳዩ የፋብሪካው አመራሮች፣ ለመላው ሠራተኞች እና ድጋፍ ላደረገው ማኔጅመንት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
